የድባቴ በሽታ ብዙ ሰዎችን በአለም ላይ ከሚያሰቃዩ የአእምሮ ህመሞች አንዱ ሲሆን ተረጂ በማጣት እና ተገቢውን እርዳታ ባለማግኘት ብዙ ሰዎቸ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ድባቴ አእምሮ ውስጥ የሚገኝ እና የሰውን የስሜት ሁኔታ የሚቆጣጠሩ ሴሮቶኒን እና ኖርኢፒነፍሪን የሚባሉ ንጥረነገሮች (ኒውሮትራንስሚተርስ) ሲዛቡ ወይንም በመጠን ሲቀንሱ የሚፈጠር ህመም ሲሆን። በተለያዩ መንገዶች ድምር ውጤት የሚከሰት ነው እነዚህም፡
- ከላይ የተቀሰው የንጥረነገር መዛባት
- በዘር የመጋለጥ እድል
- ግላዊ እና ማህበራዊ ሁኔታዎች ናቸው(የሚወዱትን ማጣት፣ ከባድ አስተዳደግ ወዘተ)
- ሴቶች የበለጠ የመጠቃት እድል አላቸው
- በእድሜ ሃያዎቹ መጀመሪያ እና አርባዎቹ ውስጥ የሚገኝ ሰው
- ያላገባ ሰው
- የአልኮል ሱስ መኖር
- ሌሎች የአእምሮ ህመሞች በተጓዳኝ ሲኖሩ
ድባቴ አለ ብሎ ለማረጋገጥ ሁለት ዋነኛ ምልክቶችን ሃኪሞች ይመከታሉ። እነዚህ ምልክቶች ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት ጸንተው መቆየት አለባቸው፦
- የፍላጎት ማጣት፡ ሌላ ጊዜ የሚያዝናና እና የሚያሰደስቱ የነበሩ ክንውኖች እንዳለ ደስታ መስጠት ሲያቆሙ
- የመደበር ስሜት፡ ብዙውን ጊዜ እና ብዙዎቹ ቀናት ላይ የሚሰማ ከፍተኛ የሃዘን ስሜት እና መደበር
ከዚህ ተጨማሪ ያሉ ምልክቶች፡
- እንቅልፍ ማጣት ወይም በጣም ማብዛት
- የሰውነት ክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
- ተስፋ የመቁረጥ ስሜት
- መድከም እና ስራ ለመስራት አቅም ማጣት
- ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት
- ዋጋ ቢስ የመሆን ስሜት
- ራስን የመጉዳት ወይም የመግደል ፍላጎት ናቸው ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የታማሚውን፣ የግል ግንኙነት ስራ እና ማህበራዊ ኑሮ ሲያውክ ድባቴ ተብሎ ይወሰዳል።
ድባቴን ለማከም የተለያዩ የህክምና መንገዶችን በአንድ ላይ መተግበር እና ከፍተኛ የሆነ ከቤተሰብ እና ከጓደኛ የሚጠበቅ ግዳፍ ያስፈልጋል። ድባቴን በህክምና መቆጣጠር ይቻላል ነገር ግን በተለያዩ ሁኔታዎች ህመሙ ሊያገረሽ ስለሚችል በትእግስት እና በቅንነት ታካሚውን መርዳት ተገቢ ነው።
- የመድሃኒት ህክምና - Fluoxetine , Sertraline, Escitalopram, Amitriptyline
- የንግግር ህክምና - ባህሪይ እና አስተሳስብ ለውጥ ላይ ያተኮረ
- በጋራ የሚደረግ የንግግር ህክምና ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ህክምናዎች ተስፋ ባለመቁረጥ መከታተል ህመሙን ተቆጣጥረው የተለመዱ የኑሮ ሂድትን እንዲያከናውኑ ይረዳል።
This information is for awareness only and does not replace a doctor's advice.